የአሸባሪው ህወሃትን ጥቃት ለማምከን የደሴና አካባቢው ህዝብ ከመከላከያ ጎን ተሰልፏል

ደሴ፣ ጥቅምት ፱ ቀን ፳፼፲፬ ( የኢት .ድ) አሸባሪው ህወሃት በደቡብ ወሎ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን የጥፋት ድርጊት ለማስቆም የደሴ ከተማ ወጣቶችና ህዝቡ ከሃገር መከላከያ ሰራዊትና ከልዩ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ እየታገሉ እንደሆነ የከተማው ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል ገለጹ።

በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚጠቀሙ አካላት የተሳሳተ መረጃዎችን ከማሰራጨት በመቆጠብ በሃላፊነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ከንቲባው አሳስበዋል።

ከንቲባው ለኢዜአ እንደገለጹት በደሴ ከተማና አካባቢው ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር እንደሌለና ህዝቡን ያሳተፈ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ ነው።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ሃገር የማፍረስ ፍላጎቱን ለማሳካት በሰላማዊ ህዝብ ህይወትና ንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመከላከልም የከተማው ነዋሪ ተደራጅቶ አካባቢውን ከመጠበቅ ባለፈ ግንባር ድረስ በመንቀሳቀስ ከሰራዊቱ ጎን እየተሰለፈ መሆኑንም አቶ አበበ ገልጸዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ ህዝቡ ወጣቱና አመራሩ በተቀናጀ መንገድ የተጠናከረ የአካባቢ ጥበቃ ከማድረግም ባለፈ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥሙ ፈጣን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ማህበረሰቡ ከተለያዩ ሃሰተኛ የመረጃ ምንጮች የሚወጡ ወሬዎችን ወደ ጎን በመተው ከጸጥታ ሃይሉ ጋር እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ሃገር ለማተራመስ ታስቦ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የሚሰራጩ ሃሰተኛ ወሬዎችን በማጋለጥና እውነተኛ መረጃዎችን በማዳረስ በኩልም መገናኛ ብዙሃን የታሪክ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሃይቅም ከተማም ሆነ በደሴ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን የገለጹት አቶ አበበ ይሄንን ሃቅ በመሸፈን ህዝብን ለማወናበድና ለመረበሽ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስረድተዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አሸባሪው ህወሃት በውጫሌና አካባቢው በፈጸመው ጥቃት 30 የሚሆኑ ንጹሐንን መግደሉን ጠቅሶ ሁሉም ወገን ከመከላከያ ጎን በመሆን እንዲመክት ጥሪ ማስተላለፉ ይታወቃል።

 

Post a Comment

አዲስ የድሮ