ዛሬ ለአገር የምናደርገው ጠብታ ነገ ትልቂቷን ኢትዮጵያ መገንባት ያስችለናል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት ፱ ቀን ፳፼፲፬ (የኢት.ድ) “እያንዳንዱ ሰው ዛሬ ለአገር የሚያደርገው ጠብታ ነገ ትልቂቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉት 1 ሺህ 496ኛውን የመውሊድ በዓል ምክንያት በማድረግ በወንድም ካሊድ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን በመገኘት ማዕድ ባጋሩበት መርሃ ግብር ላይ ነው።

በመርሃ ግብሩ ፋውንዴሽኑ ለሚረዳቸው ከ100 በላይ ከጎዳና ለተነሱ ወጣቶች ማዕድ ያጋሩ ሲሆን ለሌሎች አቅመ ደካማ ወገኖች ለበዓል መዋያ የሚሆን የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንቷ ወንድም ካሊድ የወገኖቹን ህይወት ለመቀየር እያከናወነ ያለው በጎ ተግባር በእጅጉ የሚመሰገን እንደሆነም ገልጸዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው አቅም ወገኖቹን ቢረዳ መልካም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ በተለይም በጎዳና የሚገኙ ወገኖችን የማንሳትና የመርዳት ራዕይ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከወንድም ካሊድ በጎ ምግባር ሁሉም ሊማር ይገባልም ብለዋል።

ሁሉም ዜጋ ወገኖቹን የመርዳት ድርሻ አለው ያሉት ፕሬዚዳንቷ በተለይ በበዓላት ወቅት ወገኖችን ማስታወስና መርዳት ሊለመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“ዛሬ እያንዳንዳችን የምናደረገው ጠብታ ነገ ትልቂቷን ኢትዮጵያ እንድንገነባ ይረዳናል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ በጎ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።

ከወንድም ካሊድ ከራስ በላይ ለሌሎች መኖርን መማር ይገባናል፤ እንዲህ ያለ መልካም ልብ በመያዝ ዜጎችን መርዳት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

መረዳዳትና መተጋገዝ ካለ በሰው ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ነው ያሉት ከንቲባዋ።

የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን መስራችና ባለቤት ወንድም ካሊድ እንዳለውም የፋውንዴሽኑ ትልቅ ህልም ከኢትዮጵያ ልመናን እና የጎዳና ህይወትን ታሪክ ማድረግ ነው ብሏል፡፡

ለፋውንዴሽኑ ራዕይ መሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን መወጣት አለበት የሚለው ወንድም ካሊድ ወገን ለወገኑ ደርሶ ችግርን በጋራ ከላያችን ላይ ማስወገድ ይገባል ሲል ክሏል።

ከጎዳና ሕይወት ተላቀው በፋውንዴሽኑ ስልጠና ያገኙና ራሳቸውን በመቻል ላይ የሚገኙ ወጣቶችም ሕይወታቸው መቀየሩን ገልጸዋል።

ወደ ፋውንዴሽኑ ከመምጣታቸው በፊት ለመኖር ምንም ራዕይ እንዳልነበራቸው ገልጸው አሁን ግን ሰርተው ራሳቸውን መለወጥ የሚያስችል ስነ ልቦና መያዛቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለፋውንዴሽኑ 20 በጎችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

ወንድም ካሊድ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ከ 1 ሺህ በላይ ወጣቶችን ከጎዳና በማንሳት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉ ተገልጿል።

Post a Comment

አዲስ የድሮ