በክልሉ 1 ሺህ 496ኛው የመውሊድ በዓል ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የምሳ ግብዣ በማድረግ ተከብሮ መዋሉ ተገልጿል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ ሙሃመድ በዓሉ በባህር ዳር ሲከበር በጦርነቱ ተፈናቅለው በከተማው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ከ2 ሺህ ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የምሳ ግብዣ በማድረግ ተከብሮ መዋሉን ተናግረዋል።
በደሴ ከተማ ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖችም የምግብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ በሁሉም አካባቢ ሃብት የማሰባሰብ ስራ መጀመሩንም አመልክተዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖች ወደቀያቸው እስኪመለሱ ድረስም ህዝበ ሙስሊሙ የሚያደርገውን ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ከሰሞኑ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያም ምክር ቤቱ በጥብቅ ያውግዛል ነው ያሉት ሼህ ሰይድ።
በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋና ማፈናቀል በአስቸኳይ መቆምና መንግስት አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
እየደረሰ ያለውን መፈናቀልና የህይወት መጥፋት ከማስቆም ባለፈም የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመለሱ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት አህመድ ወንዴ በበኩሉ፤ በዓሉን እያከበርን ያለነው የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መሆኑን ተናግሯል።
የተፈናቀሉ ወገኖች አካባቢያቸው ሰላም ሆኖ ወደቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ አሁን እያደረግን ያለነውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል።
”የነቢዩ መሃመድን ፈለግ በመከተል የመውሊድ በዓልን እያከበርን ያለነው የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳትና በማሰብ ነው”ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ መሪም መሀመድ ናቸው።
ለተፈናቀሉ ወገኖች የምናደርገው የምግብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ በበዓል እለት ብቻ ሳንወሰን እስከ መጨረሻው አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ሲሉም አስታውቀዋል።
በዓሉ በክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ ተከብሮ መዋሉም ተመላክቷል።
አስተያየት ይለጥፉ