ትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 መከላከል መመሪያዎችን እየተገበሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት ፱ ቀን ፳፼፲፬ (የኢት.ድ)  በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 መከላከል መመሪያን በመተግበር የመማር ማስተማር ስራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ገለፁ።

አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሙቀት መለኪያ መሳሪያና የጤና ባለሙያ እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች እንዳሉት የትምህርት ስራ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል።

ይህን ተከትሎ ትምህርት ቤቶቹ የመማር ማስተማር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ ተግባራትን በማከናወን ትምህርት እየሰጡ መሆኑን ገልፀዋል።

በፊውቸር ሆፕስ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የሚሰጡት ሲስተር ይደነቁ ምህረት እንደገለጹት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የኮቪድ-19 ክትባት ወስደዋል።

የመማሪያና የአስተዳደር ክፍሎችም የኬሚካል ርጭት ተደርጎላቸዋል።

የአሚጎንያን ትምህርት ቤት መምህር ታደለ ዘሪሁንም ትምህርት ከተጀመረበት እለት አንስቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ግቢ ከመግባታቸውና ከመውጣታቸው አስቀድሞ የሙቀት መጠናቸው እንደሚለካ ገልጸዋል።

በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ በአንድ ጠረቤዛ ሁለት ተማሪዎች ማስክ ሳያወልቁ ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ኢዜአ ተመልክቷል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ የሙቀት መጠኑ ከ37 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆነ ተማሪ ካገኙ ለይተው በማስቀመጥ አቅማቸው የሚፈቅደውን ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ቁጥር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ገነት ስዩም ወረርሽኙን ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ መማር ማስተማሩ መግባታቸውን አውስተዋል።

የተማሪዎች ምገባ ሲካሄድም ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የእሸት የቅድመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደምሰው መኮንን በበኩላቸው በትምህርት ቤታቸው ለመጋቢ እናቶችና መምህራን ክትባት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በማታና በተግባር ተኮር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተማሪዎች ክትባት እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ከቅድመ ዝግጅት በተጨማሪ ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑ የተናገሩት ደግሞ የእውቀት ለህብረት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ይታገሱ ካሳ ናቸው።

ሆኖም በትምህርት ቤቶቻቸው የጤና ባለሙያዎች ባለመኖራቸው የሙቀት ልኬቱን የሚያካሂዱት ስልጠና ያገኙ መምህራን መሆናቸውን ገልፀዋል።

ርዕሳነ መምህራኑ ትምህርት ቤቶች ከፈረቃ አሰራር ወደ ነባሩ የትምህርት አሰጣጥ በመመለሳቸው የሙቀት መለኪያ እጥረት ማጋጠሙንም ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በ2013 ትምህርት ዘመን ከ2 ሺ 700 በላይ ተጨማሪ ክፍሎችና የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የትምህርት ቤት ክሊኒክ በማደራጀት ትምህርት መጀመሩን አስታውሰዋል።

ሆኖም የጤና ባለሙያዎች ስራውን እየለቀቁ መሆኑን አንስተው በምትካቸው ለመቅጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለሁሉም ትምህርት ቤቶች አንድ የሙቀት መለኪያ መሰጠቱን ገልፀው እጥረት ካለ ትምህርት ቤቶቹ ችግሩን በራሳቸው እንዲፈቱ አሊያም ለቢሮው ሪፖርት ካደረጉ ችግሩን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከትምህርት ቤት ባለፈ ወላጆችና መላው ኅብረተሰብ በወረርሽኙ ላይ እያሳየ ካለው መዘናጋት በመታቀብ ራሱን ከኮቪድ-19 እንዲከላከልም አሳስበዋል።

Post a Comment

أحدث أقدم