ከክልሉ ጋር ተቀናጅተን በመስራት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን


 ጅግጅጋ፤ ጥቅምት ፱ ቀን ፳፼፲፬ (የኢት.ድ) ከሱማሌ ክልል ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልሰ አብዲሳ አስታወቁ።

የሱማሌ ክልል መንግስት ምስረታ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ ለተመሰረተው አዲስ መንግስት የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ አሻባሪው ህወሓት በሁለቱ ክልሎች ህዝብ መካከል የፈጠረው ሁከትና ቁርሾ በተቀናጀ መንገድ ተወግዶ ዘመን የተሻገረው የህዝብ ለህዝብ ሁለንተናዊ ትስስር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ይህን ትስስር  በፀና መሠረት ላይ በማዋቀር የክልሎቹን እና የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ከሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ጋር በመሆን የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ እንደሚረባረቡም ነው የገለጹት።

ዛሬ በተመሠረተው የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ሁለት አባላቱ በካቢኔ ደረጃ የተካተቱለት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ተፎካካሪ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሪያሌ ሃሙድ፤ በክልሉ አዲስ መንግስት በመመስረቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።


ባለፉት ሶስት ዓመታት ክልሉ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኑን ጠቅሰው ”በተለይ በሱማሌ ና በኦሮሞ ክልል ህዝቦች መካከል የነበረው  የጠነከረ ግንኙነት ወደ ቦታው እንዲመለስ መሰራቱ ያስደስታል” ብለዋል።

የተጀመሩ ለውጦችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በክልሉ ከተመሠረተው አዲሱ መንግስት ጋር ተባብረው በመስራት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በበኩላቸው፤ ከተመሠረተው የክልሉ መንግስት ጋር ተባብረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ።

 በጅግጂጋ ከተማ የተካሄደው  የሱማሌ ክልላዊመንግስት ምክር ቤት  መስራች ጉባኤ   አፈ-ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ  እንዲሁም  የክልሉን ርዕስ መስተዳደር ፣ምክትል ርዕሰ መስተዳደር በመሾም መረሃ ግብሩን አጠናቋል።

Post a Comment

أحدث أقدم