የፌዴራል መንግሥትና የዕርዳታ ድርጅቶች ለዋግ ሕዝብ በተግባር እንዲደርሱለት ጥያቄ ቀረበ

አዲስ አበበ ጥቅምት ፰ ቀን ፳፼፲፬
 ሕዝቡ ለከፋ ረሃብ መጋፈጡ ተጠቁሟል

የዋግ ልማት ማኅበር የፌዴራል መንግሥትና የዕርዳታ ድርጅቶች ከሚያካሂዷቸው ንግግሮችና ውሳኔዎች ባለፈ፣ የዋግን ሕዝብ በተግባር ደርሰው እንዲታደጉት ጠየቀ፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርበት የተገለጸው የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አብዛኛው ቦታ በአሸባሪነት በተሰየመው ሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ከዋለ ጀምሮ፣ ለከፋ የረሃብ አደጋ መጋለጡን ማኅበሩ ዓርብ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በዞኑ ከሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ሳህላና ዝቋላ ከተባሉ አካባቢዎች ውጪ፣ ቀሪዎቹ ወረዳዎች በታጣቂዎች በቄጥጥር ሥር መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ከአጠቃላይ ሕዝቡ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ቀድሞውንም በዕርዳታ እህል ይኖር እንደነበር የጠቀሱት የማኅበሩ የአዲስ አበባ ከተማ የገቢ አሰባሳቢ ዓብይ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ምትኩ በየነ፣ ቀጣናው በቁጥጥር ሥር ከዋለ ጀምሮ አንድም ዓለም አቀፍ ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ቦታው እንዳላደረሰ ተናግረዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር የሚያቀርበውን ዕርዳታ እነዚህ አካባቢዎች ኤፍኤፍኤች በተባለ ድርጅት በኩል እንዲደርስ ስምምነት የተደረሰው ከ20 ቀናት በፊት ቢሆንም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት አቅርቦት እንዳልደረሰ አክለው አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ማኅበሩ ከአገር አቀፍ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ እንዲሁም ከተለያዩ ለጋሽ ተቋማት ጋር በመሆን ወደ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ በማሰባሰብ በመጠለያ ካምፖች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፤

ከዞኑ መውጫ አጥተው በረሃብ ከሚሰቃዩት የኅብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ ቀዬአቸውን ለቀው ከአካባቢው የወጡ 100 ሺሕ ተፈናቃዮች በዘንዘልማ፣ በእብናት፣ በሳህላና በደሴ አካባቢዎች፣ እንዲሁም የተወሰኑት ደግሞ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ተጠግተው እየኖሩ እንደሆነ አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡

ሰብሳቢው በዋግ ህምራ ቆላማ አካባቢዎች መታረስ የነበረባቸው የእርሻ ቦታዎች አለመታረሳቸውንና ሕዝብ በየቤቱ የነበረው የሰብል ምርት መጠናቀቁን በመግለጽ፣ ሕዝቡ አሁንም ጨለማ ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ለዚህ በከፋ ረሃብ ውስጥ ለሚገኘው ሕዝብ በአፋጣኝ መድረስ ካልተቻለ በርካታ ሕይወት ሊጠፋ ይችላል ብለዋል፡፡

አቶ ምትኩ ምንም እንኳ የተረጋገጠ ቄጥር ማግኘት ባይቻልም፣ በረሃብ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ስለመኖራቸው ሪፖርት እንደደረሳቸው፣ የሸቀጥ መደብሮች ባዶ ቀርተው አንድ ክብሪት አንድ መቶ ብር ስለመሸጡ መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል የሕወሓት ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው የሰሜን ወሎ፣ የሰሜን ጎንደር፣ የዋግ ህምራና የደቡብ ጎንደር አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መጠጋቱን ክልሉ ማሳወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህም በተጠቀሱት አካባቢዎች በምግብና በመድኃኒት ዕጦት በርካታ ዜጎች እየተሰቃዩ  እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ጉዳዩ የህልውና በመሆኑ ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ክልሉ ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

Post a Comment

أحدث أقدم