መስከረም 20/2014 ዓ.ም. በክልሉ ከተካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኋላ ዛሬ የተመሰረተው የሱማሌ ክልላዊ መንግስት አዲሱ ምክር ቤት ሙስጠፌ መሀመድ ዑመርን ርዕሰ መስተደድር አድርጎ መሾሙን ቀደም ብሎ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከተሾሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ፤ አዲስ የተመሰረተው መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት የተገኙ ጅምር የሰላምና የልማት ለውጦችን ከዳር ለማድረስ ይረባረባል ብለዋል።
ሽብርተኛው ህወሃትና ተላላኪዎቹ ባለፉት 27 ዓመታት የክልሉን ህዝብ ሰላም ፣ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን የነጠቁበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል ።
ሆኖም ባለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት የህዝቡ ሁለንተናዊ መብቶች እየተረጋገጡለት ይገኛል ብለዋል።
እነዚህን የለውጥ ፍሬዎች ወደ ከፍታ ለማሻገር ርብርቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመረጠንን ህዝብ የልማት ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመመለስና የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ የተቀናጀ ስራ ይከናወናል ነው ያሉት።
በተለይ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማሳካት ከፌደራል መንግስትና ከክልሎች ጋር የተጀመሩ የለውጥ ዓመታት ጥረቶች ይበልጥ እንዲያብቡ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ጋር ተቀናጅቶ የመልማት፣አስተማማኝ ሰላም የማረጋገጥ ጅምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት የሱማሌና የኦሮሞ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተጀመረውን በጋራ የማደግና የመበልፀግ ጅምር ተግባራት ትርጉም ባለው መንገድ እንደሚጠናከር ተናግረዋል ።
የሚፈለገው ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲመጣ ህዝቡ ስህተቶችን በማረምና ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል ።
ምክር ቤቱ አቶ ኢብራሂም ዑስማንን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲያገለግሉ በሙሉ ድምፅ መርጧቸዋል ።
በክልሉ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ ርዕሰ መስተደድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም የሶማሌ ላንድ ከፍተኛ አመራሮች የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
إرسال تعليق